Issue 01 | Dec 2024
Concept Hub | ሀሳብ አለኝ | Magazine | Issue 01
መልዕክት
ውድ አንባቢያን ይህ ‹‹ሐሳብ አለኝ›› የተሰኘው የመጀመሪያ ዕትም ዲጂታል መጽሔት በአቀራረቡም ሆነ በአዘገጃጀቱ ለየት ያለ ሐሳብ ይዞ ብቅ ያለ ነው፡፡ የዚህ መጽሔት ዝግጅት በውስጡ ሦስት መሰረታዊ ዓላማዎችን የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥሩ ሙያዊ ክህሎትና እውቀት እንዲሁም የመጽሐፍና የማንበብ ልምድ ያላቸው ብዙ ወጣቶች ያሉ ቢሆንም ሐሳባቸውን የሚያካፍሉበት፤ የሚወያዩበት እና የሚሟገቱበት የወጣቶች መድረክ አነስተኛ በመሆኑ፥ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ለማስተዋወቅ በማሰብ የተጀመረ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሀገራችን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት እንደመሆኑ መጠን በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አቋሙን የሚያንጸባርቅበት፤ ግብዓት የሚሰጥበት፤ ድምጹን የሚያሰማበት፤ ሞያዊ ትችቶችን የሚያቀርብበት፤ የሚማማርበት፤ የንባብ ባህሉን እና የውይይት ክህሎቱን የሚያዳብርበት ነጻ መድረክ ለመፍጠር በማቀድ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሦስተኛው ወጣቱ ሐሳቡን በሰለጠነ እና በሳል በሆነ መንገድ ከመግለጽ ባለፈ የመጽሔቱ አምደኞች ክፍያ እንዲያገኙ ማስቻልና መጥቀምን፤ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተለይም በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ በመስራት ወጣቱ ዘንድ ያለውን እምቅ አቅም ማሳየት እና የሥራ ትስስሮችን መፍጠርን ግቦቹ አድርጎ ተነስቷል፡፡
በመሆኑም ይህ መጽሔት በአዘገጃጀቱ ለየት ያለ ነው ስንል፥ በዚህ መጽሔት የሚሳተፉ ጸሐፊዎች በሙሉ በሚባል መልኩ ቋሚ አምደኞች ሳይሆኑ ጹሑፋቸውን ለማሳተም የጠየቁ ወጣቶች ናቸው፤ ወደፊትም ‹‹ሐሳብ አለኝ መጽሐፍ ፈልጋለሁ›› የሚል ወጣት በሙሉ ጹሑፉን በተጠቀሱት አድራሻዎች በመላክ መሳተፍ ይችላል፡፡ በአቀራረቡም ለየት ያለ ነው ስንል ወቅትን ጠብቆ የሚወጣ መጽሔት አይደለም፡፡ ከላይ እንዳነሳነው ይህ መድረክ ለወጣቶች የተዘጋጀ አማራጭ መድረክ እንደመሆኑ እንደ እንደሚኖረው ተሳትፎ መጠን የመጽሔት ዝግጅቱም እየጨመረ የሚሄድ ይሆናል፡፡ መጽሔቱን ከማውጣት በተጨማሪም በቀረቡ ጹሑፎች ላይ ውይይቶችን በማዘጋጀት ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ያደርጋል፡፡
ይህ ከሆነ ‹‹ወጣቱን በቀላሉ የሚስቡ በርካታ መንገዶችና አማራጮች እያሉ ለምን የንባብ ልምዱ አነስተኛ በሆነበት ጊዜ በመጽሔት መልክ መምጣት አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እንደተባለውም በዚህ ወቅት የንባብ ልምዱ በተለያዩ መክንያቶች እየተቀዛቀዘ ቢሆንም ትውልድ በዚህ የማንበብ እና የመጽሐፍ ልምምድ ውስጥ ማለፉ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህም ይበልጥ የሚያዳክም ሳይሆን የሚያቀራርብ፤ እየዘመነ የሚሄድ እና የሚያነቃቃ አማራጮች ያስፈልጉታል፡፡ በዚህ መጽሔት ወጣቶች በሙያቸውና በክህሎታቸው በየአከባቢያቸው ጥናቶች እንዲያደርጉ፤ ለችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዕድል ይመቻቻል፡፡ ለዚህ ደግሞ የማንበብ አከባቢን የማስተዋልና የመጠየቅ ክህሎትን ማዳበር ሲያስፈልግ በዚህ መልኩ የተጠና የተደራጀ ሐሳብን ለማቅረብ ደግሞ መነሻው ጹሑፍ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በጹሑፍ የቀረቡ ሐሳቦች ግን በተለያዩ አማራጮች የማቅረብ ሥራ ይሰራል፡፡
በመጨረሻም ይህ የወጣቶች መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሞያቸው፤ በክህሎታቸው እና በእውቃታቸው ለሰብዓዊ መብት ክብር የሚቆሙ፤ ለማኅበረሰባዊ ንቃት የሚታገሉ፤ ስለህጻናትና ሴቶች ጥቃት ግድ የሚላቸው፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን የሚፋለሙ፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳስባቸው፤ ስለሰላም ዘብ የሚቆሙ፤ ስለትምህርት ጥራት የሚቆረቆሩ፤ ስለወጣቱ የሚሟገቱ፤ እና መሰል ንቁ ወጣቶችን እንደሚያሳየን እምነታችን ነው፤ ለዚህም ወጣቱ እንዲሳተፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡