Issue 01 | Apr 2026
የጥንካሬ እና የጽናት ተምሳሌቷ ሴት! እና ሌሎችም | Issue 01
ውድ አምባቢያን
ይህ መጽሔት በውስጡ የያዛቸው ታሪኮችና ዘገባዎች እንዲሁ በዘፈቀደ የተሰበሰቡ ሳይሆኑ፣ በታላቅ ጥንቃቄና ግልጽ በሆነ መስፈርት የተመረጡ ናቸው። ለዚህ እትም የሚሆኑ ጽሑፎችን ለማሰባሰብ ባወጣነው ግልጽ የጽሑፍ ውድድር ጥሪ፣ ከየአቅጣጫው በርካታ ተሳታፊዎች ድምፃቸውን ለማሰማት ጥረት አድርገዋል።
ይህ የጽሑፍ ውድድር ለሁሉም ክፍት የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ለህትመት የሚበቁ ሥራዎችን ስንመርጥ ሦስት መሠረታዊ መርሆችን ትኩረት አድርገን ነበር።
በመጀመሪያ፤ መስማት የተሳናቸው ወገኖቻችን በራሳቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑና የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው አንደበት እንዲተርኩ ትልቅ ዕድል ሰጥተናል። ይህ ውሳኔያችን "ስለ እኛ ያለ እኛ ተሳትፎ" የሚለውን መርህ በተግባር ለማዋልና ትክክለኛውን ድምፅ ለተደራሲያን ለማድረስ ያለመ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፤ የጋዜጠኞችን ሙያዊ አበርክቶና ሚና አክብረናል። ጋዜጠኞች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉና ብዙ ያልተባለላቸውን ጉዳዮች በሙያዊ ብቃት አቀናብረው በማቅረብ፣ የችግሩን ጥልቀትና የመፍትሔውን አቅጣጫ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያሳዩ ተደርጓል።
በሦስተኛ ደረጃ፤ እስካሁን ካልተነገሩና ከተደበቁ ታሪኮች መካከል ለሰዎች ትልቅ ትምህርትና ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎች መዝነው እንዲመረጡ ተደርጓል። እነዚህ ታሪኮች ግለሰባዊ ትግልን ብቻ ሳይሆን፣ ሰፊውን የማኅበረሰብ ግንዛቤ የሚፈትኑና አዲስ እይታን የሚሰጡ ናቸው።
ይህ አሳታፊ የሥራ ሂደት ፕሮጀክቶችንና መርሐ-ግብሮችን አካታች ከማድረግም ባለፈ፣ በዝምታ የታጠሩና ጆሮ ያላገኙ ታሪኮችን በቀላሉ ወደ ሰው ጆሮ የሚያደርሱ ድልድዮች ናቸው። በዚህ መጽሔት ውስጥ የምታገኟቸው ገጾች ሁሉ የእነዚህን ወገኖቻችንን የጽናት፣ የፈጠራና የብቃት ታሪኮች በዝርዝር የሚተርኩ ናቸው።
ይህ መጽሔት የሁላችንንም ግንዛቤ በማስፋት፣ ለተሻለና ለተሟላ አካታችነት መንገድ እንደሚከፍት ተስፋ እናደርጋለን።
መልካም ንባብ!