
ድብቁ የወሲብ ገበያ: ቴሌግራም ያቀጣጠለው የወሲብ አብዮት
በፈረንጆቹ 2013 አማራጭ የመልዕክት መለዋወጫ ሆኖ የኢንተርኔቱን አለም የተቀላቀለው ቴሌግራም ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን ማፍራት ችሏል። መተግበሪያው ቀላል፣ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑና በአንድ ቡድን ውስጥ በርካታ አባላትን መያዝ መቻሉ በብዙዎች ዘንድ ምቹ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
መተግበሪያው በሜታ ኩባንያ መተግበሪያዎች ላይ በተነሱ የደኅንነት ሥጋቶች፣ በዶናልድ ትራምፕ የማኅበራዊ ሚዲያ ዕግድ፣ በዩክሬን ራሺያ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነቶች ምክንያት ከፍተኛ ተጠቃሚዎችን ችሏል።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰፊ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ያሏት ሀገር ስትሆን በሲሚላር ዌብ ጥናት [1] መሠረት ቴሌግራም የኢትዮጵያውያን ቁጥር አንድ የመልዕክት መለዋወጫ እንደሆነ ይጠቀሳል። በዝቅተኛ የኢንተርኔት አቅም መስራት መቻሉ፣ የንግድና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ምቹ መሆኑ ቴሌግራም በኢትዮጵያ ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል።
የኮሮና ወረርሽኝ የወለደው ኢንተርኔትን መሠረት ያደረገው አዲስ የትምህርትና የሥራ ባህል በኢትዮጵያ የቴሌግራም ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል። [2] በመሆኑም የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር ጨምሮ የመንግስት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ከማህበረሰቡ ጋር ለመገናኘት ተመራጭ መንገዳቸው አድርገውታል።
ቴሌግራም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ከደንበኞች ጋር ለማገናኘት፣ ለትምህርትና ለመረጃ ልውውጥ አወንታዊ ሚናን ቢጫወትም ላልተረጋገጡ መረጃዎችና የሤራ ትንተና፣ ማንነትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች፣ ለህገወጥ ንግዶች፣ ለገንዘብ ማጭበርበርና ለመሳሰሉት ተጠቃሚዎችን ማጋለጡን የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በዚህ ፅሁፍም ቴሌግራም ከሚታማባቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ልቅ የወሲብ ገበያ ከኢትዮጵያ አንፃር እንዳስሳለን፡፡፡
ዳንኤል ከወራት በፊት እንደ ቀልድ ቴሌግራም ላይ ያገኘው የሳይበር ወሲብ አገልግሎት ሱስ እንደሆነበትና ለመውጣት እንዳዳገተው ይገልፃል።
ስሙ ዳንኤል [3] ይባላል የድሬደዋ ነዋሪና የዩንቨርስቲ ተማሪ ነው በቴሌግራም ለሚፈፀሙ የሳይበር ወሲብ [4] ተግባራት እስከ ስድስት ሺህ ብር በወራት ውስጥ እንዳወጣ ይናገራል። ዳንኤል ከወራት በፊት እንደ ቀልድ ቴሌግራም ላይ ያገኘው የሳይበር ወሲብ አገልግሎት ሱስ እንደሆነበትና ለመውጣት እንዳዳገተው ይገልፃል።
እንደ ዳንኤል ያሉ ወጣቶችን ሰለባ ያደረገው ‹‹የሳይበር ሴክስ›› አብዮት በሀገራችን ከተጀመረ ከአምስት አመት በላይ እንደሆነው ለዚሁ አላማ የተከፈቱ የአንዳንድ ቻናሎችና ግሩፖች እድሜ ይናገራል። ነገር ግን ከፍተኛ መስፋፋትን ያሳየው ከኮሮና ቫይረስ በቤት መቆየት በኋላ መሆኑን ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ዳሰሳ የተደረገባቸው የቴሌግራም ግሩፖችና ቻናሎች እንቅስቃሴ ያሳያል፡፡
በተለይም የሀገሪቱ ከፍተኛ የኢንተርኔት አቅራቢ የሆነው ኢትዮቴሌኮም ከአንድ አመት በፊት የፖርን ገጾች እንዲወርዱ [5] ካደረገ በኋላ በቴሌግራም ፖርንን መመልከትና ተያያዝ ተግባራት መስፋፋታቸውን መመልከት ተችሏል፡፡

ግሩፖቹና ቻናሎቹ ስሞቻቸውንና ዩዘርኔማቸውን ለመሠየም ወሲብ ነክ በሆኑ ቁልፍ ቃላት ሲጠቀሙ በአማካይ ከ500 አስከ 10ሺ አባላት/ተከታዮች አሏቸው፡፡
በውስጣቸውም ልክ እንደ ሲንጋፖር አቻዎቻቸው [6] አባላቶቻቸውን ከተቃራኒም ሆነ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ለአልጋማገናኘት፣ የቪዲዮ፣ የድምፅ፣ የቻት የወሲብ አገልግሎት ማቅረብ፣ የወሲብ ቪዲዮዎችን መሸጥ፣ ከባህል ተቃራኒና ፀያፍ የወሲብ ልምምዶችን በታሪክና በቪዲዮ ማለማመድ፣ ወሲብ ነክ የሆኑ መድኃኒቶችና ቁሳቁሶችን የመሸጥ ሥራ ይሠራሉ።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በተወሰኑ ግሩፕ ላይ ካሉ ምልልሶችና ውይይቶች እንደተረዳው ለዲጂታል ወሲብ አገልግሎቶች ከ500 - 3000 ብር ይጠየቃል፡፡
በዚህ የወሲብ ንግድ የተሰማሩ አካውንቶች በየጊዜው ፕሮፋይላቸውን የሚቀያይሩ ሲሆን በገጻቸው ላይ የሚገኘው ስማቸውና ክፍያ ለመፈጸም የሚጠቀሙባቸው የቴሌ ብርና የባንክ አካውንት ስያሜዎች የተለያዩና አንዳንዴም የተቃራኒ ጾታ ሲሆን እንዲህ በሚሆንበት ወቅት አካውንቱ የፍቅረኛዬ ነው፣ የወንድሜ ነው፣ የኔ እንቢ ስለሚል ነው፣ ሲሙን ያወጣሁት በሌላ ሰው ነው አይነት መሰል ምክንያቶችን ይደረድራሉ::
ለዲጂታል ወሲብ አገልግሎቶች ከ500 - 3000 ብር ይጠየቃል፡፡
በአንጻሩ የቴሌግራም ቦትን በመጠቀም ማንነታቸውን ሙሉ ለሙሉ ደብቀው የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ ብዙሃኑ የ"ሴቶች" ተብለው በተከፈቱ አካውንቶች በአብዛኛው የሚያወሩት ወንዶች መሆናቸውና ቅድሚያ አስከፍለው ብር ከተቀበሉ በኋላ ከፋዩን ብሎክ እንደሚያደርጉና አንዳንዶችም ሀሰተኛ ቪዲዮዎችን እንደሚልኩ ከምልልሱ ለመረዳት ችሏል።
የወሲብ ቪዲዮዎቹን በተመለከተ "የሀገርውስጥ" እና "የህፃናት" የሚባሉ የወሲብ ቪዲዮዎች ከፍተኛ ክፍያ የሚጠየቅባቸው ሲሆኑ ከባህል ያፈነገጡ እንዲሁም በኃይል የሚፈፀም ወሲብ (አስገድዶ መድፈርን) የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም እንዳሉ ለመታዘብ ተችሏል።
የሀገርኛ የወሲብ ክምችቶች የሚሰበሰቡት ለማስታወሻ በሚል ከፍቅረኞቻቸው ጋር የሚደረጉ አካላዊም ሆነ የኦንላይን የወሲብ ግንኙነታቸውን ከሚቀዱ ጥንዶች፣ በመፀዳጃ ቤት፣ ፔንስዮንና በመታጠቢያ ቤት ከተገጠሙ ድብቅ ካሜራዎች፣ በግድ ከሚደረጉ የቪዲዮ ቀረፃዎችና ከአንዳንድ 18+ የቪዲዮ ስትሪሚንጎች ሲሆን በቪዲዮዎቻቸው መለጠፍ ምክንያት ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡና ራሳቸውን ያጠፉ ሴቶችም እንዳሉመስማት የተለመደ ነው፡፡
አንድ በዚህ ሽያጭ የተሰማራ አካውንት ጋር በተደረገ ልውውጥ ቪዲዮው የአርቲስቶችና የታዋቂ ሰዎች ሲሆን ዋጋው እንደሚጨምር ተመልክቷል።

ሌላው እጅግ የሚያስደነግጠውና ብዙ ፈላጊ እንዳለው ለመታዘብ የተቻለው የህፃናት ወሲብ ነው። በነዚህ የወሲብ ቪዲዮዎች ላይ እድሜያቸው 15 እንኳን የማይሟላቸው ህፃናት ከአዋቂዎች ጋር ወሲብ ሲፈፅሙ የሚታዩ ሲሆን እንደዚህ አይነት ቪዲዮዎች ተፈላጊ መሆናቸው አሁን ላይ እየተባባሰ የመጣው የህፃናት የወሲብ ጥቃት ነገም ላይ ከአሁን በከፋ ላለመፈጠሩ መተማመን እንደማንችል ያስረዳናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መድፈርን የሚያበረታቱና የተደፈሩበትን ቀን እንደደስታ የቆጠሩ ባለታሪኮች እንደፃፏቸው ተደርገው የሚቀርቡና አንዳንዴም በሴቶች የሚተረኩ ወሲባዊ ታሪኮች ህፃናትን፣ የቤት ሰራተኞች፣ ዘመዶችና ተከራዮችን ትኩረት ያደረጉ ጥቃቶችንና ወሲባዊ ግፊቶችን የሚያበረታቱ ናቸው። ከባህል ተቃራኒ የሆኑ የግብረሰዶም ልምድን ከማበረታታት ባሻገር የማገናኘት ሥራም እንዲሁ ይሰራበታል፡፡
"የሀገርውስጥ" እና "የህፃናት" የሚባሉ የወሲብ ቪዲዮዎች ከፍተኛ ክፍያ የሚጠየቅባቸው ናቸው።
እነዚህ ገፆች ከህክምና ምክር ውጭ የሆኑ ያልተረጋገጡና ለሥንፈተ ወሲብና መሰል ችግሮች ይሆናሉ ተብለው የሚቀርቡ የመድኃኒቶቸ እንዲሁም የወሲብ ቁሳቁስ ሽያጭ ማስታወቂያዎች የሚሄዱባቸው ናቸው፡፡
እነዚህ መድኃኒቶች ሆነ ዕቃዎቹ ተገቢውን ህጋዊና ሞያዊ ፍተሻ ጠብቀው የማይገቡ በመሆናቸው፤ ህጋዊ መንገድን ጠብቀው ወደ ሀገር የሚገቡትም ቢሆኑም መድኃኒቶቹ ያለ ሐኪም ዕርዳታና ያለበቂ ማማከር ከተወሰዱ አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡
ሌላው በእነዚህ ገጾች ላይ የሚተላለፈው ማስታወቂያ የባህል ህክምና ነው፡፡ በባህል ህክምና ስም ለሚፈጸሙ ጉዳቶች ተጋላጭ እንደሚያደርግ ማኅበሩ በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ [7]
እነዚህ የባህል ህክምና እንደሚሰጡ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ግለሰቦች በኢትዮጵያ የባህል ህክምና አዋቂዎች ማኅበር ያልተመዘገቡና በህጋዊ ማዕቀፍ ሥር ያልታቀፉ መሆናቸውን በማስታወቂያው ላይ በተጠቀሱ ስልኮች ጋር በተደረገ የስልክ ልውውጥ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የቴሌግራምን የደህንነት ፖሊሲ ሽፋን በማድረግ የሚፈጸሙ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ወጣቶች የፖርኖግራፊ፣ ሴክስቲንግ [8] ሱስ ተጋላጭና ጥንቃቄ ለጎደለው ወሲባዊ ልምምዶች ከማድረጉ [9] ባሻገር ለህጻናትና ለጾታዊ ጥቃቶች መስፋፋት ፣ ለግለሰባዊ የነጻነት መብት ጥሰት፣ ራስን ለማጥፋትና ላጎንዮሽ የጤና ጉዳቶችና ለህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት የሚኖራቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ቢሆንም በቴሌግራም ድርጅትም ሆነ በሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ክፍሎች ትኩረት እንደተነፈገው ያሳያል፡፡
የቴሌግራም ተቋም የፖርኖግራፍ ቪዲዎችንና ወንጀሎችን ለሚለቁ ግሩች፣ ቦቶችና ቻናሎች ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት ቢፈጥርም ሪፖርቱን መሰረት አድርጎ እርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ ምናልባት ተወሰደ የሚባለው እርምጃ የማስጠንቀቂያ ምልክት በገጹ ላይ መለጠፍና ከአይኦስ (አይፎንና የአፕል ፕሮዳክቶች) ላይ ማንሳት ነው፡፡
ነገር ግን የቴሌግራም ፋይሎች በቀላሉ የሚጋሩና ከጠፉ በኋላ ጭምር በክላውድ የማይደመሰሱ [10] በመሆናቸው ከዚህ የከፋ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ዕንዲያደርግና ቴሌግራም የሀገሪቱን ህግና የተጠቃሚዎችን ደህንነት እንዲጠበቅ የማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የአውሮፓ ህብረትና ብራዚል እንዳደረጉት [11] ሁሉ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተቋሙ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይገባል፡፡ ከዘህ ባሻገር ቤተሰብ የልጆቻቸውን የስልክና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሊቆጣጠሩና ግለሰቦች ግላዊነታቸውንና ደህንነታቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
[3]ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ
[4]ሳይበር ሴክስ በኢንተርኔቱ አለም ለሚካሄዱና አካላዊ ላልሆኑ ግንኙቶች የተሰጠ ስያሜ ሲሆን በውስጡ የሳይበር የወሲብ ንግድ (Cyber prostitution)፣ ሴክስቲንግ፣ ፎንሴክስ፣ ሊቭ ሴክስና cyber pornን የሚያጠቃልል ቃል ነው። https://www.smsna.org/patients/did-you-know/what-is-cybersex
[5] https://www.linkedin.com/posts/birukfekadu_porn-activity-7113625220761952256-vvYV/
[6] https://www.straitstimes.com/singapore/telegram-channels-offer-explicit-sex-videos-photos-for-a-fee-in-similar-vein-to-sg-nasi-lemak
[8]ወሲባዊ መልዕክቶችን የመላላክ
[9] Sexting and high sexual risk-takingbehaviours among school youth innorthern Ethiopia: estimating usingprevalence ratio፡ https://sci-hub.se/10.1136/bmjsrh-2018-200085