ወጣት ዲፕሎማቶች ለምን የሉንም ?
ኢትዮጵያ በዓለም-አቀፍ መድረኮች የሚወክሏትን ወጣት ዲፕሎማቶች ለምን አጣች? አልፎ አልፎስ የምናያቸው ወጣቶች ቶሎ ከእይታችን የሚጠፉበት ምክንያት ምንድነው?
የዚህ ጹሑፍ መነሻ ሐሳብ ኢትዮጵያ ባላት የወጣቶች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትመደብ ሀገር ሆና ሳለ ነገር ግን ወጣቶቿ በፖለቲካዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና ሌሎች ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ነው ተብሎ ስለሚወቀስ፤ አልፎም የዲፕሎማሲው ሥራ ለወጣቶች ያልተፈቀደ በሚመስል መልኩ የመሳል አዝማሚያ ስለሚስተዋል ምን ይሆን ምክንያቱ? ምንስ መደረግ አለበት? ሲል የሚመለከታቸውን አካላት ቃለመጠይቅ በማድረግ ‹‹ለምን ? ›› የሚል ጥያቄ በአንባቢያን ዘንድ ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም በምትወከልባቸው ዓለማቀፍ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ወጣት ማየት ከባድ ነው። የዲፕሎማሲው ዘርፍ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በጉልህ እየታዩ ባሉ ፈተናዎች ውስጥ በብዙ የተፈተነችበት ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ዲፕሎማሲያችን ምን ያክል ውጤታማ ነው የሚለውን ምዘና ለጊዜው ብናቆየው እንኳን ዘመኑን የዋጀ እና ዘመኑን የመሠሉ በሳል ወጣት ዲፕሎማቶች ወደፊት ቀርበው አለመታየታቸው ግን የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም የዲፕሎማሲ ፖሊሲያችን በሰፊው ትችት ይቀርብበታል።
አልፎ አልፎ በዚህ ዘርፍ አሉ ተብለው የምናያቸው ወጣቶች ስያሜውን ከፊት የመለጠፍ አባዜ እንጂ በብቁ የሰለጠኑና ቦታው የሚመጥነውን ክህሎት ያሟሉ ሆነው አይታዩም፡፡ አልፎ አልፎ የምናያቸው ብቁ ወጣቶች ደግሞ በዚሁ መስመር ሲቀጥሉ አይስተዋልም፡፡
በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም በምትወከልባቸው ዓለማቀፍ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ወጣት ማየት ከባድ ነው
አሁን ላይ በበይነ መረብ እና በሌሎች አማረጮች የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ለመስራት ጥረት ከሚያደርጉ ወጣቶች መካከል ያነጋገርናት ወጣት ሳምራዊት ክፍሉ "ወጣቶች በዲፕሎማሲው ዘርፍ የመስራት አቅም እና ብቃቱ እንደሌላቸው መታሰቡ እንዲሁም በዘርፉ በዕድሜ መብሰል ከሌሎቹ መስፈርቶች በተለየ መልኩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ ወጣቶች ወደፊት እንዳይመጡ አድርጓል ብዬ አምናለሁ" ትላለች፡፡
"በዚህም ምክንያት ወጣቱ ጋር ያለውን አቅም በውጪ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲው በኩል መጠቀም እንዳንችል አድርጎናል፤ በተለይም መንግስት ከሰልጠና ጀምሮ ለወጠቶች እድሉን ከመፍጠር አኳያ ብዙ የሚጠበቅበት ቢሆንም በተግባር ግን እምብዛም አይስተዋልም" ትላለች፡፡
ፖለቲከኛው አቶ ጌትነት ወርቁ የሄው ጉዳይ አብዝቶ እንደሚያሳስባቸው ነግረውናል። "በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ኤምባሲዎች እንዲሁም የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ውስጥ በርካታ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነገር ቢሆንም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም በምትወከልባቸው ዓለማቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ውስጥ ግን ኢትዮጵያዊ ወጣት ማየት ከባድ ነው"
"በሀገራችን ዲፕሎማቶችን ከታች ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ የማብቃት እና መንገዱን እንዲያውቁት የማድረግ ልምድ የለም፤ ይህም በዲፕሎማሲው ዘርፍ እንደ አገር ይበልጥ ደካማ እየሆንን እንድንሄድ እያደረገን ይገኛል" ብለዋል፡፡
በተጨማሪም "ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያየ ጉዳዮች ላይ ያጋጠሙንን አለማቀፍ ጫናዎች በመደበኛው የዲፕሎማሲ አቅም መወጣት ሳይቻል በቀረበት ጊዜ በግል ተነሳሽነት በዲፕሎማሲ ስራ ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ወጣቶች ያመጡትን ውጤት ማስታወስ በቂ ነው" ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡
"ነገር ግን" ይላሉ አቶ ጌትነት "እነዚህን ወጣቶች ይበልጥ እንዲበረቱ ብሎም ሌሎች ወጣቶችን እንዲያሠለጥኑ እንዲሁም በዲፕሎማሲው በኩል ከመንግስት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ከማድረግ ይልቅ ነገሮች የረገቡ ሲመስሉ ከነመፈጠራቸውም ሲረሱ ይታያል፡፡ ይህም በቀጣይ ሌሎች ወጣቶች ወደፊት እንዳይመጡ የማድረግ እድሉ ሰፊ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል" በማለት በተለይም መንግስት ትኩረት ሊሠጠው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ማሳሰቢያ አዘል የሆነ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ወጣቶች የሚፈጥሩት ንቅናቄ የተሻለ ተቀባይነት አለው
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካሪ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ በበኩላቸው "ዓለማቀፍ ጫናዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ መንግስት በራሱ ከሚያደርጋቸው የማሳመን እንቅስቃሴዎች በላቀ መልኩ በቂ እውቀት እና ችሎታው ያላቸው ወጣቶች የሚፈጥሩት ንቅናቄ የተሻለ ተቀባይነት እንዳለው የሌሎች አገራት ተሞክሮ ያሳያል" ይላሉ።
"ነገር ግን በመንግስት በኩል በተለይም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከወጣቱ ጋር ተቀራርቦ መስራት እና ዕድሉን በማመቻቸት በኩል ፍላጎት አለመኖር እና ልምድም የሌለን መሆኑ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አቅም እንዳይኖረን ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚነሳ ነው" ብለዋል።
በተለይም ደግሞ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ፍላጎቱ ያላቸውን ወጣቶች መለየት፤ ተጨማሪ ስልጠናዎችን ማመቻቸት እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ወጣቶችን ዕድል መስጠት አለበት ነው ያሉት።
በኢትዮጵያዊ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ወርቃማው ጊዜ ነው በሚባልበት 1950ዎቹ ላይ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በመሆን ያገለገሉት ከተማ ይፍሩ ስማቸው የገነነ ዲፕሎማት ነበሩ፤ ለአፍሪካ ህብረት ምስረታም የነበራቸው አስተዋፆ አሁንም ድረስ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በንጉሱ ተሹመው ከነበሩት ሚንስትሮች መካከል እርሳቸው ወጣት እንደነበሩ ይነገራል።
እድሉን መንግስት ሊፈጥር ይገባል
አቶ ሙሉጌታ ከተማ የቀድሞው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ከተማ ይፍሩ ልጅ ናቸው፤
የዓለማቀፍ ግንኙነት አማካሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ከተማ ይፍሩም ከላይ የተነሱ ሀሳቦችን በመደገፍ ወጣቶችን በዲፕሎማሲው ዘርፍ በብዛት እና በጥራትም ጭምር መፍጠር ቢቻል አሁን ዓለም እየተጓዘ ካለበት ፍጥነት እኩል መራመድ እንድንችል አስተዋጾው የጎላ ነው ይላሉ፡፡
በተለይም ደግሞ ትልልቅ የሚባሉት ዓለማቀፍ ተቋማት አሰራራቸው የተወሳሰበ እና ቢሮክራሲው የሚበዛ እንደሆነ አንስተው ይህንን ውስብስብ አሰራር ተረድቶ በፍጥነት መንገድ አበጅቶ ከመስራት አኳያ የወጣቶች አስፈላጊነት በቀላሉ የሚታይ መሆን እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡
ለዚህም "በዲፕሎማሲው ዘርፍ ብቁ ወጣቶችን ከማፍራት አኳያ በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የተግባር ልምምዶችን ማመቻቸት እና ፍላጎቱ እና አቅሙ ያለቸውን ወጣቶች ደግሞ በመለየት ለሀገር መጥቀም እንዲችሉ እድሉን መንግስት ሊፈጥር ይገባል" ሲሉ መክረዋል።
"ቀደም ባሉት ሥርአቶች ወጣቶች እንደ ተባበሩት መንግስታት ባሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ሄደው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ይደረግ ነበረ" በማለት "አሁን ደግሞ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን በእጃችን ያለውን እድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ጸሐፊ ረዳት የነበሩት ተገኘወርቅ ጌጡን(ዶ/ር) ስለዚሁ ጉዳይ አነጋግረናቸዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በኤምባሲዎች ውስጥ ወጣቶች እየሄዱ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ የማመቻቸት ስልጣኑ አለው
እርሳቸውም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ግነት የሚሰጣቸው ሀገራት ውስጥ ወጣቶች ለዘርፉ ፍላጎት እንዲኖራቸው አንዲሁም አለማቀፍ ተቋማት እንዴት ነው የሚሰሩት የሚለውን የሚያስተምሩባቸው ማዕከላትን አቋቁመው እንደሚሰሩ ገልጸው፤ ‹‹በእኛ ሀገር ግን በራሳቸው ጥረት የሚመጡት እንኳን እድሉን ሲያገኙ አይስተዋልም›› ይላሉ፡፡
"የዓለማቀፍ ተቋማትን እና አጠቃላይ የውጪ ግንኙነት ሥራዎችን ለወጣቶች ክፍት ማድረግ እና በተግባር እየተማሩ እንዲመጡ ማድረግ ያስፈልጋል፣ በተለይም ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በኤምባሲዎች ውስጥ ወጣቶች እየሄዱ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ የማመቻቸት ስልጣኑ አለው" ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ወጣቶችን ማብቃት እና ዕድሎች እንዲመቻላቸው ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
በጨማሪም መንግስትም ሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘርፉ ለአገር የሚኖረውን ጠቀሜታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ወጣቶችን ማብቃት እና ዕድሎች እንዲመቻላቸው ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ወጣት ዲፕሎማቶችን እና መሪዎችን ማብቃት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው ‹‹ሴፍ ላይት›› የተሰኘ ተቋም በማቋቋም የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት የተቋሙ ሥልጠና እና ልማት ሀላፊ አቶ ስምኦን ጌትነት ናቸው።
ተቋሙ ከተመሰረተ ከ3 ዓመት በላይ የሆነው ሲሆን በእነዚህ አመታትም በተለይም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ላይ ፍላጎቱ ያላቸውን ወጣቶች በመሰብሰብ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች ጋር እንዲገናኙ እና ልምዳቸው እንዲካፈሉ ከማድረግ በተጨማሪም አቅማቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተከታታይ ሥልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ጋር ለመስራት ጥረቶችን ቢያደርጉም በተለይ ቀጥተኛ ባለድርሻ ከሆነው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል በቂ ትኩረት አለማግኘታቸውን ያስረዳሉ።
በአገራችን ወጣቶችን በአመራርነት እንዲሁም አገርን ወክሎ በሚደረጉ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ላይ እምብዛም ተሳታፊ እንዳልሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዜሪያም ለውጥ ለማምጣት እንዲሁም ብቁ እና በአገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመስጠት አቅም ያላቸው ወጣት አመራሮችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተከታታይ የሥልጠና መድረኮችን በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚንስቴር አማካኝነት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ጥቅምት 9፣ 2016 ዓ/ም. በተካሄደ አንድ የወጣት መሪዎች ዙሪያ ባተኮረ መድክ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ወጣት አመራሮችን እና ዲፕሎማቶችን ማብቃት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ተቋማትን በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እና እገዛ ለማድረግ ማቀዳቸውንም አስታውቀው ነበር፡፡ የዚህን አፈጻጸም በዚህ ጹሑፍ ማካተት ለጊዜው ባንችልም ግን የሚታይ ነገር፤ ለውጥ መፍጠር የሚችል ነገር ግን ወጣቱም ህዝቡም ይጠብቃል፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ወደ ኋላ እየቀረች እንድትሄድ ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው ፈጣን አስተሳሰብ እና አቅም ያላቸው ወጣቶች በዘርፉ ተገቢውን ቦታ ሊሰጣቸው አለመቻሉ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ከከወጣቱም፤ መንግስትም እንዲሁም በዘርፉ ካሉ ልምድ ካካበቱ ዜጎች ‹‹ለምን ? ›› የሚል ቁጭት የሚፈጠረው መቼ ነው?
ማጣቀሻ፡
- ከተማ ይፍሩ የሰላም ዕድገትና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ፤ ሙሉጌታ ከተማ፤ 2015 ዓ/ም
- https://press.et/herald/?p=100205
- የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሀሳብ ጥቅምት 9 2016 በተካሄደው 3ኛው የወጣት መሪዎች ውድድር እና ጉባኤ መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር
- ከላይ ከተጠቀሱት ማጣቀሻዎች ውጪ በጹሑፉ የተካተቱት ቃለ መጠይቆች ከዚህ ጸሑፍ አዘጋጅ ጋር የተደረጉ ናቸው፡፡